• ኢትዮ 360

በአፋር ክልል የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም ተጠየቀ።

Updated: Dec 21, 2019

በአፋር የመከላከያ ተሽከርካሪዎችን አቃጥላችኋል በሚል ሰበብ ወጣቶችና የመብት ተሟጋቾችን ለማሰር የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል።-የክልሉ ነዋሪዎች.በአፋር የመከላከያ ተሽከርካሪዎችን አቃጥላችኋል በሚል ወጣቶችና የመብት ተሟጋቾችን ለማሰር የተጀመረው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል ሲሉ የክልሉ ነዋሪዎች ጠየቁ።


ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንዳሉት በቅርቡ በአፋርና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ከተነሳው አለመግባባት ጋር በተያያዘ ግጭት ተቀስቅሷል።


ሁለቱ ክልሎች አንዱ አካባቢ ድርቅ ሲገባ ወደ ሌላኛው ክልል ገብቶ የግጦሽ ሳርን መጠቀም በሚለው ሃሳብ ላይ ተግባብተው ሲተገብሩት ቆይተዋል።


ለውጥ መጣ መባሉን ተከትሎ ግን ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ነዋሪዎች በስፍራው ቤት ገንብተው የእኛ ቦታ ነው ወደ ማለት መሄዳቸው ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት ነው ይላሉ።


በግጭቱ ከሁለቱም ወገኞች ሰዎች መጎዳታቸውን ለኢትዮ 360 መራጃውን ያደረሱት ነዋሪዎች ይናገራሉ።


የተጎዱ ሰዎችን ለማንሳት የሔደ አንድ ወጣት በመከላከያ ጥይት ተመቶ መገደሉ ደግሞ የአፋር አርብቶ አደሮችን ያስቆጣ ክስተት ነበር።

ለምን በየጊዜው እንገደላለን፣ለምንጠይቀውስ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠን አካል ማነው ሲሉ ጥያቄ ያቀርባሉ።


በየጊዜው የአፋር ወጣቶችን በጥይት እየፈጀ ያለው የመከላከያ ሰራዊት በህግ ተጠያቂ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንዴት ሌላውን ህብረተሰብ በህግ ተጠየቅ ማለት ይቻላል ሲሉም ይጠይቃሉ።


ይሄንን ክስተት መነሻ አድርጎ ደግሞ የአስተዳደሩን ችግር ለሚመለከተው አካል እያጋለጡ ያሉና ለመብታቸው እየታገሉ ያሉ የአፋር ወጣቶችን ሰበብ ፈልጎ ለማሰር የሚኬድበት ርቀት አግባብ አይደለም ብለዋል።


የፌደራል መንግስቱም ሆነ የሚመለክታቸው አካላት የክልሉ አመራሮችና የመከላከያ ሰራዊቱ በንጹሃን የአፋር ልጆች ላይ ሊወስዱት ያቀዱት ርምጃን ሊያስቆሙ ይገባል ሲሉ በኢትዮ 360 በኩል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።


ኢትዮ 360 ከአፋር ነዋሪዎች የተነሳውን ቅሬታ ይዞ ከሁለቱም ወገኖች ያሉ አመራሮችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሊሳካለት አልቻለም።

281 views0 comments