• ኢትዮ 360

በሞጣ የ4 መስጊዶች መቃጠል የሀይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ያለመ ነው ተባለ።

Updated: Dec 23, 2019

amharic date goes here


በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ የመስጊዶች ቃጠሎ የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ ያለመ ወንጀል በመሆኑ እንደሚያወግዙት የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

Photograph by Ahmedin Jebel

ለኢትዮ 360 የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳደረሱት መረጃ ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ከቀኑ 11 ሰአት አካባቢ በሞጣ ከተማ በሚገኘው የጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ እሳት ይነሳል።


በእሳት አደጋውም በመቅደስ ውስጥ የነበሩት ነዋየ ቅድሳት መቃጠላቸውን ይናገራሉ።


እሳቱን የአካባቢው ነዋሪ ተረባርቦ ካጠፋ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር የአካባቢው ፖሊስ የነበረውን ግርግር ማርገቡን ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ወደቤታቸው እንዲገቡ ማድረጉንም ነው የገለጹት።


በዚያው ቀን ምሽት ግን 2 ሰአት ተኩል አካባቢ አራት መስጊዶችና ማርዘነብ ሆቴል እንዲሁም ከሶስት በላይ ሱቆች መቃጠላቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።


አደጋው በምሽት ከመቀስቀሱ ጋር ተያይዞ እሳቱን ቶሎ ማጥፋት አለመቻሉንም ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮ 360 የገለጹት።

በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የተነሳው እሳት ካህናቱ እዛው በነበሩበት ሰአት የተነሳ በመሆኑ በሆነ ስህተት የተፈጠረ እንጂ የማንም ጣልቃ ገብነት ሊኖረው አይችልም ሲሉም ግምታቸውን ተናግረዋል።


ከመስጊዶቹና ከሆቴሉ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ከከተማዋ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የተጻፈው ደብዳቤ ምክንያት ሊሆን ይችላልም ሲሉም ጥርጣሪያቸውን ይገልጻሉ።


ከምክር ቤቱ የተጻፈው ደብዳቤ በሆቴሉ ውስጥ ሌላ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች በሚስጥር ስብሰባ እያደረጉ መሆኑን የሚገልጽ ነው።


እናም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሚስጥራዊ ስብሰባው እየተካሄደ ያለው ከእስልምና ምክር ቤቱ እውቅና ውጪ በመሆኑና ሌላ አደጋ ከማስከተሉ በፊት ተከታትለው ርምጃ እንዲወስዱ በደብዳቤው መጠየቁን ጠቁመዋል።-ይሄ ባይሆንና ችግር ቢከሰት ሃላፊነቱን እንደማይወስድ የእስልምና ምክር ቤቱ አስታውቆ ነበር።


እንደ ነዋሪዎቹ አባባል የትላንቱ አደጋ ከነዚህ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ ሳይሆን አይቀርም ባይ ናቸው።


ዛሬ ማለዳ ላይ በአካባቢው የደረሰው የፌደራሉ የፖሊስ ሃይል አካባቢውን በማረጋጋትና የአደጋውን መንስኤ በማጣራት ላይ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።


For more information, watch now:543 views0 comments