• ኢትዮ 360

የወላይታ ዞን ሕዝብ ላቀረበው የዞንነት ጥያቄ እየተሰጠው ያለው የሃይል እርምጃ አስቆጥቶታል።- ነዋሪዎች

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 21/2012) የወላይታ ዞን ሕዝብ ላቀረበው የዞንነት ጥያቄ እየተሰጠው ያለው የሃይል እርምጃ እንዳስቆጣው ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንደገለጹት በዞኑ የተሰማራው የጸጥታ ሃይል ነዋሪውን መተንፈሻ አሳጥቶታል።

በላባቸው ሰርተው የሚኖሩ የቀን ሰራተኞች ሁሌም ስራ ከሚጠባበቁበት ቦታ አትቁሙ በሚል በጸጥታ ሃይሉ የሚደርስባቸው ድብደባ የነዋሪውን ትዕግስት እየተፈታተነው ነው ያላሉ።

ከምሽቱ ሁለት ሰአት ጀምሮ ምንም አይነት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በሚል የተላለፈው ውሳኔ የዞኑን ኢኮኖሚ ሽባ እንዳደረገውም ይገልጻሉ።

የዞኑ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ላቀረቡት ጥያቄ እየተሰጣቸው ያለው ምላሽ በዱላ መሆኑ እንዳስቆጣቸው ይናገራሉ።

ከምሽቱ ሶስት ሰኣአት በኋላ አንድም ሰው በአካባቢው ሲንቀሳቀስ መገኘት የለበትም በሚል የተቀመጠው ሰአት እላፊም ዞኑ ሰላም እንዲርቀው አድርጎታል ይላሉ።

ኢትዮ 360 በወላይታ ህዝብ የመብት ጥያቄና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ክልሉ ምን እያደረገ ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱን ለማነጋገር ሞክሮ ከአስር ደቂቃ በኋላ ደውሉልኝ የሚል ምላሽ ቢሰጠውም፣በሰአቱ ሲደወልላቸው ግን ስልካቸውን ከመዝጋት ውጪ ለምላሹ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም።


14 views0 comments