• ኢትዮ 360

አረና በምርጫው እንዳይወዳደር ለማድረግ ህወሃት እየሰራ ነው። ሊቀመንበሩ አቶ አብርሃ ደስታ

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 24/2012) አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዲሞክራሲ በምርጫው እንዳይወዳደር ለማድረግ ህወሃት እየሰራ ነው ሲሉ ሊቀመንበሩ አቶ አብርሃ ደስታ ገለጹ።

የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት በግልጽ ተቃዋሚ አንፈልግም ብለው አውጀዋል የሚሉት አቶ አብርሃ ይሄ ማለት አረና በትግራይ ክልል መወዳደር አይችልም ማለት ነው ሲሉ ከኢትዮ 360 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ህወሃት ፓርቲያቸውን አሸባሪ፣ህገ መንግስቱን ለመናድ የተነሳ በሚል መፈረጁንም ተከትሎ በፓርቲያቸው ላይ እየተደረገ ያለው ማስፈራራትና ዛቻ መቀጠሉን ይናገራሉ።

በተደጋጋሚም በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደረገው እስርና ድብደባም የዚሁ አካል ነው ይላሉ አቶ አብርሃ ደስታ።

ለአንድ ወር ታስረውና ሲደበድቡ ቆይተው የተለቀቁት 13 እስረኞች የዚህ ማሳያ ሲሆኑ ለአንድ ወርና ለሁለት ወር እየታሰሩና እየተደበደቡ የሚለቀቁ አባላቶቻቸው ቁጥር ግን ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።-አሁንም አራት አባሎችቸው በእስር እየማቀቁ መሆኑን በመጠቆም።

በሕወሃት ፍረጃ ውስጥ የተካተተው አረና ብቻ ሳይሆን ህወሃትን የማይደግፍ የትግራይ ህዝብ ሁሉ ባንዳ ተብሏል ነው ያሉት።

ዛሬ ላይ ግን የህወሃት ግፍ ያንገሸገሸው ወጣት ለመብቱ ሊታገል መነሳቱን ነው የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ የሚናገሩት።

ወደ አምስት ሺ አባላት አሉን የሚሉት አቶ አብርሃ ህወሃት የሚያደርስባቸውን ግፍና ጭቆና የሕይወት መስዋዕትነት እስከ መክፈል ባለው ደረጃ ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በፌደራል ደረጃ መንግስት አለ ብለው እንደማያምኑ የተናገሩት አቶ አብርሃ እየደረሰባቸው ያለውን እንግልትና መከራም ለማንም አቤት ማለት እንደማይችሉም በግልጽ አስቀምጠዋል።

መንግስት የሚባለው አካል ሃገርን እየመራሁ ነው ካለ ለራሱ ክብር የሚሮጠውን ነገር ትቶ ለህዝብ ክብር ቢሰራ ውጤት ማምጣት ይችላል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ የትግራይ ህብን በአማራጭ ለማገልገል እያደረኩት ያለው ትግልን እንዳላራምድ ተደርጊያለሁ ሲል ህወሃትን መክሰሱም ታውቋል።


51 views0 comments