• ኢትዮ 360

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ሃገር ካሉ ችግሮች ጋር በተያያዘ ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚል መብት የለውም።- የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ


(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 22/2012) ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ሃገር ካሉ ችግሮች ጋር በተያያዘ ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚል መብት እንደሌለው የቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ አስታወቁ።

የቦርዱ አቅም ውስን ነው ያሉት የኮሚኒኬሽን አማካሪዋ ወይዘሪት ሶሊያና የቦርዱ ሃላፊነት ምርጫው በተወሰነለት የጊዜ ገደብ ማካሄድና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ መስጠት ነው ብለዋል።

ይሄ ማለት ግን ቦርዱን ኣንደ ሃገር ያሉ ችግሮች አያሳስቡትም ማለት አይደለም ብለዋል ከኢትዮ 360 ጋር በነበራቸው ቆይታ።

የምርጫ አስፈጻሚዎችን በየቦታው ከማሰማራት ጀምሮ ቦርዱ በየክልሎቹ ከሚያከናውናቸው ተግባራት ጋር በተያያዘ የጸጥታ ጉዳዩ ይመለከተዋል ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ቦርዱ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመወያየት የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት ይሞክራል ባይ ናቸው።

ቦርዱ ከመጀመሪያው ጀምሮ የያዘውን ምርጫውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የማካሄድ አቋሙን አሁንም ይዞ ይቀጥላል ብለዋል።

ቦርዱ አሁን ላይ ጠንካራ አቋም ላይ ነው ማለት ባይቻልም ያሉበትን ውሱንነቶች በመቅረፍ ስራውን ግልጽ በሆነ መልኩ ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ምርጫውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማካሄድ የምርጫ ቦርዱ ሃላፊነት ብቻ አይደለም ይላሉ።-- ሌሎች አካላትም በምርጫው እንደሚሳተፉ በመጠቆም

የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ መመሪያ አንመዘገብም ብለው ያቀረቡት ቅሬታንም ተመልክቶ ወደ 74 የሚደርሱ ፓርቲዎች በቀደመው መመሪያ እንዲመዘገቡ ተደርገዋል ብለዋል።

ፓርቲዎቹ በቀደመው መመሪያ እንዲመዘገቡ የተደረገው የቀድሞ መመሪያ የሚጠይቀውን ማስረጃ በማቅረባቸውና ህግን ወደ ኋላ መልሶ ተቀበሉ ማለት ስለማይቻል ነው ብለዋል።

የምርጫ ማካሄጃ የጊዜ ቀነ ገደብንም ሆነ አዲሱን መመሪያ በቀጣዩ ሳምንት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም የምርጫ ቦርዱ የኮሚኒኬሽን አማካሪ ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።

25 views0 comments