• ኢትዮ 360

በጅማ ዩኒቨርስቲ የተጀመረው የትምህርት ማቆም አድማ ቀጥሏል።-የኢትዮ 360 ምንጮች


(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 22/2012) በጅማ ዩኒቨርስቲ የተጀመረው የትምህርት ማቆም አድማ መቀጠሉ ተሰማ።

በዩኒቨርስቲው አድማውን እያደረጉ ያሉት የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ተማሪዎች መሆናቸውን ነው የኢትዮ 360 የመረጃ ምንጮች የሚናገሩት።

በዋናነት የትምህርት አድማው የተጀመረው የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች በክልላቸው መመደብ አለባቸው የሚል ነው።

እንደ ኢትዮ 360 ምንጮች ተማሪዎቹ ወደ ክልላቸው ተመልሰው ካልተመደቡ ትምህርት አንጀምርም የሚል አቋም መያዛቸው ነው የተገለጸው።

ከዚህም ሌላ ይሄንን የትምህርት ማቆም አድማ እየመራ ያለውና ራሱን ቄሮ ብሎ የሚጠራው ቡድን በግቢው ውስጥ ያሉ ሁሉም ተማሪዎ እስከ ታህሳስ 25/2012 ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ግቢው ውስጥ እንዲበተን ባደረገው ወረቀት አማካኝነት ትዕዛዙን አስተላልፏል።

ይሄ ደብዳቤ መበተኑን ተከትሎም በግቢው ያሉ ተማሪዎች በጭንቀት ላይ መሆናቸውን ነው ምንጮቹ ያመለከቱት።

በግቢው ያለውን የጸጥታ ችግር ፈርተው በርካታ ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለሳቸውን ነው የመረጃ ምንጮቹ ለኢትዮ 360 የገለጹት።

ከተማሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይት ቢያደርግም ውጤት ማምጣት አልቻለም የተባለው የዩኒቨርስቲው ሴኔት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሴኔቱን ውሳኔ ከሰሙ በኋላ ግቢውን ለቀው ለመውጣት የተዘጋጁት ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንም የመረጃ ምንጮቹ ገልጸዋል።

21 views0 comments