• ኢትዮ 360

በደቡብ ጎንደር ዞን ከቤንሻንጉልና ኦሮሚያ አዋሳኝ የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆች የሚረዳቸው አተው እየተሰቃዩ ነው።-ኢትዮ 360 መረጃ

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 21/2012) በደቡብ ጎንደር ዞን በደብረታቦር ከተማ ከቤንሻንጉልና ኦሮሚያ አዋሳኝ ተፈናቅለው በአካባቢው የሰፈሩ የአማራ ክልል ተወላጆች የሚረዳቸው አተው እየተሰቃዩ መሆኑን ገለጹ።

ተፈናቃዮቹ ከኦሮሚያና ከቤንሻንጉል አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈናቅለው ከመጡ አመት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

በአንድ አመት ውስጥ አራት ጊዜ ከተሰጣቸው በአንድ ሰው 15 ኪሎ ስንዴና ግማሽ ሊትር ዘይት ውጪ ምንም አይነት ድጋፍ አለማየታቸውን ነው ለኢትዮ 360 በምሬት የሚናገሩት።

ለዞኑም ሆነ ለእምባ ጠባቂ ተቋም ያስገቧቸው ደብዳቤዎችና ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ።

በየአብያተ ክርስቲያናት ለመጠለል የሚያደርጉት ሙከራም በጸጥታ ሃይሉ ድብደባ እንዲበተን እንደሚደረግ ይናገራሉ።

በቤንሻንጉል ካማሽ ዞንም ሆነ በኦሮሚያ ደምቢዶሎ አካባቢ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና እንግልት አሁንም አላቆመም ይላሉ።

አምና ከቦታው ሲፈናቀሉ ከ360 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንና ሰሞኑንም በዛው አካባቢ ሶስት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉን ነው የሚጠቁሙት።

በአማራ ክልል ምላሽ ማግኘት ያልቻሉ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ለመመለስ ያደረጉት ጥረትም ዋጋ እያስከፈላቸው ነው ብለዋል ለኢትዮ 360።-ከሰሞኑ አንደኛው ተፈናቃይ አንድ እጁ ተቆርጦ መመለሱን ነው ተፈናቃዮቹ ጨምረው የሚናገሩት።

ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ወደ ዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ስዩም ኢትዮ 360 ያደረገው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።4 views0 comments