• ኢትዮ 360

በወሎ ዩኒቨርስቲ ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።- የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 24/2012) በወሎ ዩኒቨርስቲ ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አባተ ጌታሁን ለኢትዮ 360 እንዳሉት ትላንት ማለዳ በዩኒቨርስቲው ለተቀሰቀሰውና ለአንድ ተማሪ ህይወት መጥፋት ብሎም ለሌሎች መቁሰል ምክንያት ለሆነው ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ ተባባሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ እንደተጠናቀቀም መረጃው ለህዝቡ ይፋ ይሆናል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ ችግሮች መፈጠር የጀመሩት በ2008 ነው የሚሉት ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አባተ ጌታሁን እነዚህ ግጭቶች የብሔር መልክን እንዲይዙ ማድረግ ከተጀመረ ግን አንድ ወር ይሆነዋል ብለዋል።

ይህንኑ ልዩነት ተከትሎ በታህሳስ 3/2012 በግቢው በተቀሰቀሰው ግጭት 6 ተማሪዎች ሲጎዱ ከማካከላቸው የአንዱ ተማሪ ከባድ ጉዳት ስለነበር በህክምናም ሳይድን ቀርቶ ህይወቱ ማለፉ ይናገራሉ።

ይህንን ጸብ ለመፍታትም በየጊዜው የሃይማኖት አባቶችና አዛውንቶች በእርቅ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ውጤት ያመጣ ቢመስልም ዘላቂነት ግን ሊኖረው አልቻለም ይላሉ።

በግቢው ትላንት የተፈጠረው ግጭትም የዚሁ ማሳያ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በሃዘኔታ ይገልጻሉ።

በዩኒቨርስቲው ትላንት የተፈጠረው ግጭት መነሻ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ተኩል ላይ ሁለት ተማሪዎች ወደ ቁርስ በመሄድ ላይ ሳሉ የተፈጸመባቸው ጥቃት ነበር ይላሉ።

በዚህም ጥቃት አንደኛው ተማሪ ወደ ህክምና ጣቢያ ቢወሰድም ጉዳቱ ከባድ ስለነበር ከረፋዱ 5 ሰአት አካባቢ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል ብለዋል።

በግጭቱ በግቢው ውስጥ በግንባታ ስራ የተሰማራ አንድ ኢንጅነር ጆሮ ግንዱ ላይ በድንጋይ ሲመታ ሌላውም የጸጥታ ሰራተኛ እንዲሁ ጉዳት ደርሶበት የጥቃቱ ሰለባ ሆነው በሆስፒታል እየተረዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት አብዛኛው ተማሪ ችግር የለበትም።በየጊዜው ችግሮች የሚፈጠሩት ጥቂት በሚባሉ ተማሪዎች ነው።

እንደዚህ አይነት ተማሪዎች የሚፈጥሩት ችግር በአማራ ክልል 10 እንዲሁም በኦሮሚያ 12 ዩኒቨርስቲዎች ላይ አለመረጋጋት እንዲኖር አድርገዋል ይላሉ።

ዛሬ በዩኒቨርስቲው ፈተና የሚጀመርበት ቀን እንደነበር የሚገልጹት ፕሬዝዳንቱ ነገሮች እስኪረጋጉ የመማር ማስተማሩ ስራ አልተጀምረም ብለዋል።16 views0 comments