• ኢትዮ 360

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙና በድሬደዋ ዩኒቨርስቲዎች ተከሰተ የተባለው ችግር በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚራገበው ወሬ አይደለም። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 22/2012) በኦሮሚያ ክልል በሚገኙና በድሬደዋ ዩኒቨርስቲዎች ተከሰተ የተባለው ችግር በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚራገበው ወሬ አይደለም ሲል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ክፍል ሃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንደሚሉት በዩኒቨርስቲዎቹ ችግሮቹ አሉ ነገር ግን ችግሮቹ መገናኛ ብዙሃኑ እያወሩት ባሉበት ልክ አይደለም።

በዩኒርስቲዎቹ ትምህርት ተቋርጧል እየተባለ የሚነዛው ወሬም ትክክለኛ ያልሆነና አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች በሰላማዊ መንገድ የመማር ማስተማሩን ስራ እያከናወኑ ነው ሲሉ መረጃዎቹን አስተባብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎቹ ከ25 በላይ ተማሪዎች ሞተዋል ተብሎ የሚነገረውም ነገር ሃሰት ነው የሞቱት 10 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎቹ በየቀኑ ከሚፈጠሩት ችግሮች ጋር በተያያዘ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚደርሱት መረጃዎች የተለያዩ በመሆናቸው በግጭቶች የተጎዱ ተማሪዎችንም ሆነ የተፈናቀሉትን ቁጥር ማስቀመጥ አይቻልም ሲሉ ምላሽ ሰተዋል።

ከዩኒቨርስቲዎቹ የወጡ የአማራም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ተማሪዎቹ ራሳቸው ተደዋውለው ወደ ዩኒቨርስቲዎቹ እየተመለሱ ነው የሚሉት አቶ ደቻሳ ምን ያህል ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው እንደተመለሱ ግን መናገር አልቻሉም።

ከኦሮሚያ ክልል የአማራ ተማሪዎች ወጡ እንደሚባለው ሁሉ ከአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች የወጡ የኦሮሞ ተማሪዎች ይኖራሉ።

ስለዚህ እንዲህ አይነት ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የሚነዙ የብሔር አጀንዳዎችን ለማስቆም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎቹ ችግር የሚፈጥሩ ተማሪዎችንም ሆነ የዩኒቨርስቲው አመራሮችና ሰራተኞች ላይ ህጋዊ ርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎቹ የፌደራል ሃይልን ከመመደብ ጀምሮ የሰአት እላፊ ገደብ እስከማስቀመጥ ያሉ ስራዎችን በማከናወን በዩኒቨርስቲዎቹ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ ነው ብለዋል ለኢትዮ 360።

የሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ይህን ይበሉ እንጂ ከዩኒቨርስቲዎቹ የተፈናቀሉ፣ሕይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ያጡ፣ለአካል ጉዳት የተዳረጉና እስካሁን የገቡበት ያልታወቀ ተማሪዎችን ቁጥር በቅርቡ ከአማራ ተማሪዎች ህብረትና ከተማሪዎቹ ኮሚቴ ያገኘንውን መረጃ ማቅረባችን ይታወሳል።7 views0 comments