• ኢትዮ 360

በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ በሕገወጥ መንገድ የሚካሄደው መሬት ወረራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መቷል።-የአካባቢው ነዋሪዎች

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 21/2012) በአዲስ አበባ ከተማ ሰሚት አካባቢ በሕገወጥ መንገድ የሚካሄደው መሬት ወረራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንዳሉት በአካባቢው በማህበር ተደራጅተው ቦታውን ያገኙት በ1985 በደርግ ዘመን ነበር።

ሰሚት ፌል ስቶን ሪል ስቴት አካባቢ ቤት የመገንባቱን ስራ ጨርሰው በአካባቢው መኖር የጀመሩትም ከ1995 ጀምሮ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

አሁን ላይ ግን ከየት እንደመጡ የማይታወቅ ወጣቶች በቡድን በመሆን አካባቢው የእኛ የእርሻ ቦታ ነበር በሚል ያገኙትን ክፍት ቦታ ሁሉ በማጠር ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ቦታውን ማጠር ብቻ ሳይሆን በገዛ ፈቃዳቸው ቤቶችን እየገነቡ መሆኑን ይናገራሉ።

የቤት ግንባታውን ሲያካሂዱ ደግሞ ለነዋሪዎቹ መውጫ መንገድ እንኳን ሳያስቀሩ ነው በማለት ሃዘናቸውን ይገልጻሉ ነዋሪዎቹ።

ከዛሬ ነገ ምን ይመጣብን ይሆን በሚል በፍርሃት ውስጥ ያለው ነዋሪ የቦሌ ክፍለ ከተማ ለዚህ ጉዳይ ብቻ በሚል ባቋቋመው ልዩ ችሎት ሁከት ይታገድልን አቤቱታ ቢያቀርቡም ከችሎቱ ያገኙት ምላሽ ዝም ብላችሁ ተከራከሩ ሁከት ይወገድልኝ ማለት አትችሉም የሚል ነው።

ለችሎቱ ወጣቶቹ እየሰሩ ያሉትን ህገወጥ ተግባር ለማስረዳት ቢሞክሩም ከችሎቱ የተሰጣቸው አጭር ምላሽ መብታቸው ነው የሚል መሆኑን ይናገራሉ።

ለችሎቱ ሃሳባችንን ለማስረዳት ብንሞክርም በቋንቋ እንኳን መግባባት አልቻልንም ብለዋል ነዋሪዎቹ በምሬት።

ለቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 አመራሮችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አቤት ብንልም ምላሹ ከችሎቱ ጋር ተመሳሳይ ነው።መብታቸውን ነው የገኙትን ባዶ ቦታ ሁሉ ማጠር ይችላሉ የሚል ነው።

በግቢያችን ያለው ቦታ ሳይቀር ታጥሮ ቤት ተሰርቶበታል የሚሉት ነዋሪዎች መንግስት ለአረንጓዴ ልማት በሚል ያጠረው ቦታም በነዚሁ ወጣቶች ተሸንሽኖ ቤት ተሰርቶበታል ይላሉ።

ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360 እንዳሉት በሃገር ውስጥ መንግስትና ህግ አለ የሚባል ከሆነ ለእነሱ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

አሁን መሬታቸውን ነገ ደግሞ ሕይወታቸውን ሊነጥቃቸው ከተዘጋጀ አካል ጋር ተፋጠው እንደሚገኙ የተናገሩት ነዋሪዎች የከፋ አደጋ ላይ ከመውደቃቸው በፊት የሚመለከተው አካል እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በዚህ አካባቢ ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በስፋት እየተፈጸመ መሆኑን ኢትዮ 360 በቅርቡ መዘገቡ ይታወሳል።
18 views0 comments