• ኢትዮ 360

በአምቦ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎችና በፌደራል ሃይሎች መካከል በተነሳው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች በርካቶች ተጎዱ።-ኢትዮ 360 ምንጮች

(ኢትዮ 360 - ታህሳስ 21/2012) በአምቦ ዩኒቨርስቲ በተማሪዎችና በፌደራል ሃይሎች መካከል በተነሳው ግጭት ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መጎዳታቸውን መረጃዎች አመለከቱ።

በአካባቢው የነበሩት ተማሪዎች ለኢትዮ 360 እንዳደረሱት መረጃ ከሆነ ችግሩ የተቀሰቀሰው ታህሳስ 1/2012 አራት ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች በስለት ተወግተው ወደ ክሊኒክ ይወሰዳሉ።

ይህንን ጉዳት ያደረሱ ተማሪዎች ደግሞ ተሰብስበው እንዲታሰሩ ይደረጋል።

ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የታሰሩት ተማሪዎች በአስቸኳይ ይፈቱ በሚል ባለፈው ረቡዕ በግቢው ውስጥ ግርግር ለመፍጠር መሞከሩንም ነው ተማሪዎች የሚናገሩት።

ትላንት ጠዋት ላይ በግቢው የተፈጠረው ተቃውሞም ተማሪዎቹ ይፈቱ አለበለዛም ትምህርት አንማርም የሚል ነው።

ተማሪዎቹን ለማረጋጋት በግቢው ተሰማርቶ የነበረው የፌደራሉ ሃይል ምንም አይነት መሳሪያ በእጁ ላይ እንዳልነበር ነው ተማሪዎቹ የሚናገሩት።

በዚህ መካከል የተማሪዎቹ የተቃውሞ ጩህት ወደ ድንጋይ ውርወራ መቀየሩንና የድንጋይ ውርወራው ደግሞ በፌደራል ሃይሉና በተማሪዎች መካከል መካሄዱን ነው የገለጹት።

በኮብል ስቶን የተደገፈው ጥቃት ከሁለቱም ወገኖች ከባድ ጉዳት ማድረሱንና የተማሪው ሃይል በጥቃቱ እየበረታ በመምጣቱ ባዶ እጁን ወደ ግቢው የገባው የፌደራል ሃይል ግቢውን ለቆ ወደ ካምፕ እንዲሸሽ መገደዱን ነው የአይን እማኝ ተማሪዎች ለኢትዮ 360 የተናገሩት።

የፌደራል ሃይሉን ከግቢ ያስወጡት ተማሪዎች ድል አደረግን በሚል ስሜት ሲጨፍሩ እንድነበርም ተማሪዎቹ የጠቁማሉ።

በዩኒቨርስቲው ስላለው ሁኔታ መረጃ የደረሰውና ከነሙሉ ትጥቁ ወደ ግቢው የገባውን ሃይል የተመለከቱትና በጭፈራ ላይ የነበሩት ተማሪዎች በየቦታው መበታተናቸው ነው የተገለጸው።

ነገር ግን ከግቢው ወቶ የነበረው የፌደራል ሃይል ራሱን አደራጅቶ ከተመለሰ በኋላ በግቢው በአጋጣሚ የተገኘ አንድም ተማሪ ሳይቀር መደብደቡን ነው የሚናገሩት።

እንደ አይን እማኞቹ ተማሪዎች አባባል አንድ የተማሪዎች ዶርም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።

በሮች ተግነጣጥለዋል፣እቃዎች ተሰባብረዋል፣በማደሪያው የተገኘው ተማሪ ሁሉ ተደብድቧል ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ በየደረጃው የሚገኘው ደም ምስክር ነው ይላሉ።

ወደ ክሊኒክ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለማየት ሞክረን ነበር የሚሉት ተማሪዎች ክሊኒኩ ቁጥሩ በማይታወቅና በተጎዱ ተማሪዎች መጨናነቁን ማየታቸውን ይናገራሉ።

አሁን ላይ ቁርጠኛ አቋሙን ያሳየው የፌደራል ሃይሉ በግቢው አንዳችም አይነት እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጓል ይላሉ።

የግቢው ትምህርት ከተቋረጠ ቆይቷል የሚሉት ተማሪዎች በመሃል የፈተና ወቅት ነው በሚል ለትንሽ ቀናት ትምህርቱ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ትምህርቱ መቋረጡን ለኢትዮ 360 ገልጸዋል።8 views0 comments